ፕሬዝዳንት ቮልዲሚር ዘለንስኪ ሩሲያ ባካሄደችው አጠቃላይ ወረራ 31 ሺ የዩክሬን ወታደሮች ተገድለዋል ሲሉ አስታውቀዋል። የዩክሬን ፕሬዝዳንት በውጊየው የቆሰሉትን ወታደሮች ቁጥር ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል። የዩክሬን ባለስልጣናት የተጎጂዎችን ቁጥር በይፋ የማይናገሩ ሲሆን ሌሎች ግምቶች ግን የተጎጂዎች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የፕሬዝዳንቱ መረጃ የተሰማው የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትሩ ለዩክሬን ምዕራባውያኑ የሚሰጡት ዕርዳታ ግማሹ በመዘግየቱ የሕይወት ዋጋ እያስከፈለን ነው ካሉ በኋላ ነው።የዘሌንስኪ መግለጫ የተጋነነ የዩክሬን ወታደሮች ሞት በሩሲያ በኩል ለተሰጠው አሃዝ ምላሽ እንደሆነ ተሰምቷል። “በዚህ ጦርነት 31,000 የዩክሬን ወታደሮች ሞተዋል። ሩሲያ እንደምትለው 300 ሺ ወይም 150 ሺ አይደሉም ፑቲን የሚናገሩት ውሸት ነው” ሲሉ አክለዋል።
በጦርነቱ ውስጥ ስላለው ሰፊ ኪሳራ የተናገሩት ዘለንስኪ እንዳሉት በሩስያ በተያዙት የዩክሬን አካባቢዎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎች ሞተዋል ነገር ግን ትክክለኛው ቁጥራቸው አይታወቅም ሲሉ አክለዋል። “ስንቶቹ እንደተገደሉ፣ ስንቶች እንደተሰቃዩ እና ስንቶቹ እንደተሰደዱ አላውቅም ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት በነሀሴ ወር የተገደሉ የዩክሬን ወታደሮች ቁጥር ከ70 ሺ እስከ 120 ሺ ሊደርስ እንደሚችል ማሳወቁ ይታወሳል።
ዩክሬን ከደረሰባት ኪሳራ ሩሲያ የከፋ ነው ያሉት ዘሌንስኪ 180 ሺ የሩስያ ወታደሮች መሞታቸውን እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን ተናግረዋል። የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር በበኩሉ 350 ሺ ወታደሮች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን አንስተዋል።ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ወታደሮች ከምስራቃዊ ቁልፍ ከሆነችው አቪዲቪካ ከተማ ለቀው መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን ለሩሲያ በጦርነቱ ከወራት በኋላ የተመዘገበ ትልቁ ድል ነው።
ዘለንስኪ በከፊል የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ አቅርቦትን በመዳከሙ የመጣ ሽንፈት ነው ሲሉ ወቅሰዋል። የባይደን አስተዳደር በበኩሉ ለዩክሬን የ 60 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ ፓኬጅ በኮንግረሱ መቆየቱ ለከተማይቱ በሩሲያ እጅ መያዝ አስተዋጽኦ አድርጓል ብሏል። ሩሲያ ሙሉ በሙሉ ወረራ ከጀመረች ሁለት ዓመታት ማስቆጠሯን ተከትሎ የምዕራባውያን ሀገራት መሪዎች ከዩክሬን ጋር ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት ቅዳሜ ወደ ኪየቭ ተጉዘዋል። በዚህም መሰረት ጣሊያን እና ካናዳ ከዩክሬን ጋር የጸጥታ ስምምነት መፈራረማቸው ተነግሯል።
በስምኦን ደረጄ





