photo_2024-01-30_10-06-19

ጥር 21፤2016 – የአሶሳ ከተማ  ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት እንዳማረራቸዉ ገለፁ

 

የአሶሳ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አልበሽር መሀመድ ከበጋ ወቅቱ  ጋር ተያይዞ የውሃ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ እና የከተማው ስፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት መጨመሩ ችግሩን እንዳስከተለው ተናግረዋል።

ስማቸዉ እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንዳንድ  የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎቹ  መንግስት  አንድ ሊለን ይገባል ዉሃ የምናገኘዉ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ነዉ ሲሉ ሃሳባቸዉን ለብስራት ቴሌቪዥንና ራዲዮ ገልፀዋል ።

በዚህም ምክንያት ዉሃ ለማግኘት እስከ 4 ስዓት ወረፋ እንደሚጠብቁ ሃሳባቸዉን ገልፀዉ ፣የዉሃ ስርጭቱ ፍትሐዊነት እንዳልሆነ ተናግረዋል።የእለት ከዕለት ኑሯቸዉን ለማስኬድ እጅግ እንደተቸገሩ ጨምረዉ ለጣቢያችን ገልፀዋል።

የአሶሳ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ዋና ሥራ አስኪያጅ  ከበጋ ወቅቱ  ጋር ተያይዞ የውሃ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ እና የከተማው ስፋት ጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ለሁሉም  የከተማው ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ውሀን ተደራሽ ማድረግ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል። በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ለተከታታይ ሁለት ቀናት ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

አቶ አልበሽር አክለው ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እስከሚገኝ  ያለውን የውሃ ምርት በአግባቡ በመጠቀም ለሁሉም የከተማው ነዋሪ ማህበረሰብ በፍትሐዊነት ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ችግሩ እንዳለ አምኖ የአሶሳ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል ።

በበቀለ ጌታሁን

photo_2024-01-29_16-53-23

ጥር 20፤2016 – የውቅሮ ከተማ ምክር ቤት ከመጠን በላይ ድግስ ደጋሾችን ለመቅጣት የሚያስችል ህግ አፀደቀ

 

የውቅሮ ከተማ ም/ቤት የ4ኛ ዓመት 37ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ይህንኑ ህግ ማፅደቁን ብስራት ሬዲዮና ቴሌቨዥን ከትግራይ ምስራቃዊ ዞን ኮሚኒኬሽን ፅህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመላክታል።

ምክርቤቱ በመደበኛ ጉባኤው የፀጥታ ጉዳዮች፣ስራ አጥነት፣ድርቅና የንፁሕ መጠጥ ዉሀ እጥረት የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል። ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ድግስ በሚል ሰበብ ከፍተኛ የሆነ ብክነት እየተስተዋለ ነው የተባለ ሲሆን እነዚህን ችግሮችን ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ እንደሚሰራየውቅሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉ ማሩ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ህዝብ ከፍተኛ በሆነ ችግር ውስጥ እያለና  በድርቅ ወቅት ከመጠን ያለፈ ድግስ የሚደግሱ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ የውቅሮ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትለወርቅ አበበ ገልፀዋል።

ነገር ግን ቅጣቱ ምንድን ነው ስለሚለው ጉዳይ የተገለፀ ነገር የለም።

በሚሊዮን ሙሴ

ጥር 20፤2016 – እኔ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ብሆን ኖሮ ወታደሮቻችን አይገደሉም ነበር ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ

 

በያዝነው አመት መጨረሻ ለሚካሄደው ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ለመሆን የሚወዳደሩት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥቃቱ “ እኔ ፕሬዝዳንት ብሆን በጭራሽ አይከሰትም ነበር” ብለዋል።ትራምፕ ይህንን ይበሉ እንጂ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸዉ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ውጥረት ከባድ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከ2016 እስከ 2020 በነበራዉ የትራምፕ አገዛዝ በሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎች አራት ወታደሮችን የገደለውን ጨምሮ ብዙ ጊዜ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ኢራን በሶሪያ ዮርዳኖስ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ በተፈጸመዉ ጥቃት ሶስት የአሜሪካ ወታደሮችን ተገድለዉ 34ቱን ለቆሰሉበት የሰው አልባ አውሮፕላኖች ድብደባ እጄ የለበትም ስትል አስታዉቃለች።የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃቱን የፈጸሙት በሶሪያ እና ኢራቅ በሚንቀሳቀሱት በኢራን የሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖች ነው ብለዋል። “መልስ እንሰጣለን” ሲሉም ዝተዋል፡፡

በየመን የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ጄራልድ ፌየርስቴይን ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን ተጨማሪ ዉጥረት ከሚያባብስ ድርጊት እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል፡፡ የአሜሪካ አስተዳደር በአካባቢው በሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ እንዲያጠናክር ከፍተኛ ጫና እንደሚደርስበት ተናግሯል።ነገር ግን ፌይርስታይን አንዳንድ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ጥሪ እንዳደረጉት ፕሬዝዳንት ባይደን በኢራን ላይ ቀጥተኛ ጥቃት እስከማድረግ ድረስ መሄድ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የየመኑ አማፂ ቡድን የሁቲ ንቅናቄ እሁድ አመሻሹ ላይ በኤደን ባህረ ሰላጤ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሙን አስታዉቋል።የወታደራዊ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሪያ በሰጡት መግለጫ፥ በኢራን የሚደገፈው ቡድን የባህር ሃይል ኢላማ ያደረገ ጥቃትን አድርሷል፡፡

በስምኦን ደረጄ

Screenshot 2024-01-29 154404

ጥር 20፤2016 – በተለምዶ”ሿሿ” የተባለውን ወንጀል  ሲፈጽሙ የነበሩ ሦስት ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ሲያዙ አንደኛዋ ወንጀል ፈፃሚ በክትትል መያዟን አዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን የፈጸሙት ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 በተለምዶ ወሎ ሰፈር ሸዋ ሱፐር ማርኬት አካባቢ ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ ነው። ወንጀል ፈፃሚዎቹ  ኮድ 1- 09609 ትግ በሆነ ሚኒባስ ሁለቱ ሴቶች ተሳፋሪ አንደኛው ረዳት በመምሰል የግል ተበዳይ የሆነቸውን ወ/ት ሌሊሴ ያደታን ካሳፈሩ በኋላ አንደኛዋ ወንጀል ፈፃሚ ያመማት በመስመሰል  የግል ተበዳይ ላይ ምራቅ በመትፋት ሌሎቹ ደግሞ የሚጠርጉ መስለው ግምቱ 40ሺ ብር የሚያወጣ የእጅ ስልኳን ከሰረቁ በኋላ  ከመኪናው ላይ ገፍትረው በማስወረድ ያመልጣሉ፡፡

የግል ተበዳይ ያሰማችውን የድረሱልኝ ጥሪ የሰሙ በወንጀል መከላካል ስራ ላይ የነበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እና በአካባቢው በነበሩ ግለሰቦች ትብብር ሦስቱ ወንጀል ፈፃሚዎች ከግል ተበዳይ ከሰረቁት ሞባይል ስልክ እንዲሁም አንድ ሌላ ተጨማሪ ስልክ  እጅ ከፍንጅ እንደተያዙ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የላንቻ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አስታውቋል፡፡

ፖሊስ ባደረገው ክትትል እንደኛዋን ወንጀል ፈፃሚ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ መቀጠሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ደጋጋሚ መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ፖሊስ አስታውቋል።

ተመሳሳይ ወንጀሎችን አስቀድሞ ለመከላከል ህብረተሠቡ ትራንስፖርት ሲጠቀም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ ለፀጥታ አካላት ማሳወቅ እንዳለበት ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

photo_2024-01-29_14-46-04

ጥር 20፤2016 – በደቡብ ሱዳን ወሬ ያበዛሉ በሚል በሀገሪቱ ሚኒስትር ስም የተሰየመው የጂን መጠጥ ጥቅም ላይ እንዳይውል ተከለከለ

 

በደቡብ ሱዳን የመካከለኛው ኢኳቶሪያ ግዛት ባለስልጣናት በአካባቢው ለመጠጥነት የሚቀርበውን ጂን በርካቶች ከጠጡ በኃል ህይወታቻው በማለፉ ምርቱ እንዳይሸጥ አገዱ።

“ማኩኢ ጂን” በመባል የሚታወቀው ሮያል ጂን በአብዛኛው ወጣቶች ዘንድ ሱስ የሚያስይዝ ነው ተብሎ ተለይቷል። የገና እና የዘመን መለወጫ በዓላት ላይ የፍጆታ መጠኑ እየጨመረ በመምጣቱ ቁጥራቸው ላልተገለጸ ሰዎች የሞት ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

ይህንኑ ተከትሎ ባለስልጣናት “ማኩኢ” የሚባለውን ሮያል ጂን የተባለውን ቀይ ቢራ ጥቅን ላይ እንዳይውል ከልክለዋል። የማዕከላዊ ኢኳቶሪያ ግዛት አስተዳዳሪ ኢማኑኤል አዲል አንቶኒ እንደተናገሩት ማንም ሰው መጠጡን መሸጥም ሆነ መጠጣት የለበትም ምክንያቱም ብዙ ወጣቶችን እየገደለ ነው ብለዋል።
በርካታ ወጣቶች ሲሰክሩ እናቶቻቸውን በገጀራ ይመታሉ ሲሉም አክለዋል። በዋና ከተማዋ ጁባ የሚገኘው የአንግሊካን ቤተክርስቲያን እገዳው ተግባራዊ ስለመሆኑ መንግስት እንዲያረጋግጥ አሳስቧል። ይህው ጂን በ 2019 ዓመት በማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሚካኤል ማኩኢ ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።

እኚህ ሚኒስትር በደቡብ ሱዳን ከሚገኙ ፖለቲከኞች በጣም ተናጋሪ ሚኒስትር በመሆናቸው ህዝቡ የጂን መጠጡን በእርሳቸው ስም ሰይሞታል። ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት ጂን ከገበያ እንዲታገድ ጠይቀው የሚያመርተው ፋብሪካ እንዲዘጋ ጥሪ አቅርበው ነበር።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-01-29_15-31-16

ጥር 20፤2016 – በመኮሮኒ ውስጥ አደንዛዥ ዕፅ ደብቆ ተጠርጣሪ ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሄደው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

 

ግለሰቡ ከናቢስ የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ ይዞ በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ጓደኛውን ለመጠየቅ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ያቀናል፡፡

ከክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ ጓደኛውን ለመጠየቅ ምግብ ይዞለት የሄደው ይኸው ተጠርጣሪ ይህንኑ ተግባር ፈፅሟል፡፡

በወቅቱ በሳህን የተቋጠረው ምግብ እንጀራ ፍርፍር በማካሮኒ ነበር፡፡ በእነዚያ የማካሮኒ ቀዳዳዎች ውስጥ የሚያብለጨልጩ ነገሮች ተወታትፈዋል፡፡

ምግቡን ፈትሸው የሚያስገቡት የፖሊስ አባላት ባዩት ነገር ይጠራጠራሉ። ምግቡ ተዘርግፎ ሲፈተሽ ብዛቱ 51 የማካሮኒ ፍሬዎች በተጠቀለሉ የአልሙኒየም ወረቀቶች አባብጠዋል፡፡

ወረቀቶቹን በመፍታት ለማየት ሲሞከርም ካናቢስ የተባለው አደንዛዥ ዕፅ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ግለሰቡ ከዚህ በፊት በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ በዚያው ፖሊስ መምሪያ ታስሮ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ድፍረት በተቀላቀለበት ሁኔታ አደንዛዥ ዕፁን በምግብ ውስጥ ደብቆ ወደ ተጠርጣሪ ማቆያ ቤት ለማስገባት የሞከረው ጠያቂ ሰዎች የሚበዙበትን ሠዓት በማጥናትና የፖሊስ አባላት በዚያ ሰዓት ሊዘናጉ ይችላሉ ብሎ በማሰብ መሆኑም ታውቋል፡፡

በፈፀመው ወንጀል የምርመራ መዝገብ ተደራጅቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡

ጥር 17፤2016 – እስራኤል ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በመሻከሩ ከቴለቪቭ ወደ ጆሃንስበርግ የሚደረገው በረራ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ ሊሰረዝ ነው

 

👉 በጋዛ ሰርጥ ከ26 ሺ በላይ ፍልስጥኤማውያን ተገድለዋል

የሃማስ እስራኤል ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በእስራኤል ጦር በተወሰደ እርምጃ ቢያንስ 26 ሺ 083 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 64 ሺ 4 መቶ 87 ሰዎች ቆስለዋል።

የሀማስ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ቢያንስ 183 ሰዎች መገደላቸውንና 377 ሰዎች መቁሰላቸውን በሪፖርቱ አመላክቷል።የእስራኤል ጦር በበኩሉ በጋዛ ሰርጥ በኩል ያሉ አካባቢዎችን በየብስ፣ በአየር እና በባህር ላይ ማጥቃት እንደሚቀጥል አረጋግጧል። የአየር ኃይሉ የፍልስጤም ተዋጊዎች ንብረት የሆኑትን የዘመቻ ማዕከላትን፣ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ስፍራዎችን፣ የመመልከቻ ቦታዎችን እና የፀረ ታንክ ኬላ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልጿል።

የባህር ሃይሉ በባህር ዳርቻው ላይ በርካታ ኢላማዎችን መምታቱን ተናግሯል። የወታደራዊው የአረብ ሚዲያ ቃል አቀባይ አቪቻይ አድራይ በደቡብ ካን ዮኒስ ከባድ ውጊያ መቀጠሉን አረጋግጠዋል። ነገር ግን እስራኤላውያን በአካባቢው በሚገኙ ሆስፒታሎች እና መጠለያዎች ላይ እየደረሰ ስላለው ጥቃት ምንም የተናገሩት የለም። ይህም በርካታ ፍልስጤማውያንን በድጋሚ ከግዛቱ ሳይወጡ ነገር ግን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ አስገድዷቸዋል።

በሌላ በኩል የእስራኤል አየር መንገድ ኤል አል በቴል አቪቭ እና በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ከተማ የሚያደርገውን የቀጥታ በረራ ሊሰርዝ መሆኑን የእስራኤሉ የዜና ወኪል ቻናል 12 ዘግቧል። በሁለቱ ከተሞች መካከል የነበረው የኤል አል በረራ ከወርሃ ሚያዚያ 1 ጀምሮ ይሰረዛል።

አየር መንገዱ ይህንን እርምጃ የወሰደው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ባለበት ሁኔታ የደንበኞች ፍላጎት መቀነስ ተከትሎ ነው።ደቡብ አፍሪካ እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅማለች ስትል ለአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ክስ ካቀረበች በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።

የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ዳኞች እስራኤል በጋዛ ውስጥ የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንድታቆም የሚያስገድድ ትእዛዝ ለመስጠት እና ከሌሎች “የአደጋ ጊዜ እርምጃዎች” ጋር በተያያዘ በዛሬ እለት ውሳኔ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።

በስምኦን ደረጄ

photo_2024-01-26_15-55-33

ጥር 17፤2016 – ለስምንት ወራት የመንግስት ሰራተኛ ላልሆነች ግለሰብ የመንግስት ሰራተኛ ከሆነዉ ባለቤቷ ጋር በመተባበር ደሞዝ ሲከፍሉ የነበሩት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

 

በባሌ ዞን ጋስራ ወረዳ የጋሰራ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ሰራተኛ ናት በማለት ደሞዝ ሲከፍሉ የነበሩ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ።

ለስምንት ወራት ወርሃዊ ደሞዝ ሲከፍሉ የነበሩት የጋሰራ ወረዳ የፋይናንስ ኃለፊዎች እና ተባባሪዎች በእስራት መቀጣታቸውን የጋሰራ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ምርምራ ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር መሃመድ ሃጂ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

አንደኛ ተከሳሽ የጋሰራ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት የሂሳብ ሰራተኛ የሆነው ሀሰን አብዱል ቃድር የተባለው ግለሰብ፣  ሁለተኛ ተከሳሽ የተከሳሿ ባለቤት የሆነዉ የጋስራ ጽ/ቤት ሰራተኛ  ፣ ሶስተኛ ተከሳሽ የሁለተኛ ተከሳሽ ባለቤት የሆነችዉ ወ/ሮ መስታዉት ፣ አራተኛ ተከሳሽ  አሰፋ ንጋቱ የወረዳዉ ትምህርት ቤቶች መምህራን ሃላፊ እና አምስተኛ  ተካሳሽ  የማዘጋጃ ቤት ሰራተኛ በመሆን ድርጊቱን መፈጸማቸው ተረጋግጧል።

ለሁለተኛ ተከሳሽ ባለቤት ለሆኑት ወይዘሮ መስታወት ተሾመ የጋስራ ወረዳ ት/ት ጽ/ቤት ሰራተኛ ናቸው በማለት በወር 8 ሺህ ብር ለስምንት ወር እንዲከፈላቸው ሲያደርጉ መቆየታቸው በማስረጃ ተረጋግጧል ።  የባሌ ዞን ፖሊስ በተከሳሾች ላይ በሙስና ክስ መስርቶ ከዓቃቢ ህግ ጋር የመዝገቡን አጣርቶ ለፍርድ ቤት ይልካል።

ክሱን ሲመለከት የነበረው የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት  ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውሳኔ አሰተላልፏል። 1ኛ ተከሳሽ በስምንት ዓመት እስራት እና በ20 ሺህ ብር ፣ 2ተኛ  ተከሳሽ   በ5 ዓመት እስራት እና በ10ሺህ ብር ፣ 3ኛተከሳሽ  ያለዓግባብ ደሞዝ በመቀበል 2 ዓመት እስራት እና 5ሺህ ብር  እንድትቀጣ ወስኗል፡፡

በተጨማሪም 4ተኛ ተከሳሽ በ2 ዓመት እና 5 ሺህ ብር ፣ 5ተኛ ተከሳሽ በ1 ዓመት እና በ5 ሺህ እንዲቀጡ  ውሳኔ መተላለፉን ምክትል ኢንስፔክተር መሃመድ ሃጂ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

ጥር 17፤2016 – የቀዶ ህክምና ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ታካሚዎች የአለርት ሆስፒታል ከሮታሪ ፋዉንዴሽን ጋር በመሆን ነጻ የህክምና ዘመቻ ህክምና ሊሰጥ ነው

 

ሮታሪ ፋውንዴሽን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ሲሆን በተለያዩ ሃገራት በመዟዞር የጤና እና ሌሎች የበጎ አድራጎት ስራዎችን የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡ ቀዶ ህክምና ለማድረግ የሚጠባበቁ ታካሚዎች በመኖራቸው ሮታሪ ሜዲከል ኬር በዘመቻ ህክምናው የታካሚዎችን ወረፋ በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የአለርት ሆስፒታል የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አቶ አለምሰገድ ጫኔ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን ተናግረዋል፡፡

የቀዶ ህክምናው የሚሰጠው ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ታካሚዎች ሲሆን የአጥንታ፤ ፕላስቲክ፤ ጠቅላላ ቀዶ ህክምና ፤የዓይን እና ሌሎች በሆስፒታሉ የሚሰጡ የቀዶ ህክምና አይነቶች መሆናቸው ተነግሯል፡፡አቶ አለምሰገድ አያይዘውም በዚህ የቀዶ ህክምና ተጠቃሚ የሚሆኑ ታካዎች ጠቅላላ ወጪያቸው ይሸፈናል ብለዋል፡፡

ከግንቦት መጀመሪያ አንስቶ ለተከታታይ 11 ቀናት የሚሰጠው ቀዶ ህክምና ከህንድ ሃገር ከሚመጡ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በአለርት ሆስፒታል ህክምናዉ በጋራ ይሰጣል፡፡የህክምና መሳሪያዎችን እና ግብአቶችን ድጋፍ ለማድረግ እንዲሁም ለባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት ከሆስፒታሉ የበላይ አመራሮች እና የተለያዩ የህክምና ክፍል ሃላፊዎች ጋር የቅድመ-ዝግጅት ውይይቶችን እና ስምምነቶች ተደርገዋል፡፡

በትግስት ላቀዉ

ጥር 17፤2016 – አላባማ በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በናይትሮጅን ጋዝ የሞት ቅጣት ፈፀመች

 

በአላባማ ግዛት በነፍሰ ማጥፋት የተከሰሰውን ኬኔት ዩጂን ስሚዝ የተባለውን ግለሰብ በናይትሮጅን ጋዝ የገደለች ሲሆን ይህም የሞት ቅጣት ዘዴ በአሜሪካ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል። የ58 አመቱ ስሚዝ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለት የመጨረሻ ይግባኝ እና ለፌዴራሉ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ያቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት አጥቷል።

የሟቹ ጠበቆች ግድያውን ጭካኔ የተሞላበት እና ያልተለመደ ቅጣት ነው በማለት ተከራክረው ነበር። እ.ኤ.አ. በ2022 የአላባማ ግዛት ስሚዝን ገዳይ በሆነ መርፌ በመውጋት የሞት ቅጣቱን ለማስፈፀም ሞክሮ አልተሳካለትም። እ.ኤ.አ. በ1989 ኤልዛቤት ሴኔት የተባለችውን ግለሰብን በመግደል ወንጀል ተከሷል። የሞት ቅጣት መረጃ ማእከል፣ ስሚዝ በአለም ላይ በናይትሮጅን ጋዝ ጥቅም ላይ በማዋል የተገደለ የመጀመሪያው የሞት ፍርደኛ ሰው ሆኗል።
አላባማ እና ሌሎች ሁለት የአሜሪካ ግዛቶች ናይትሮጅን ሃይፖክሲያ እንደ አማራጭ የሞት ቅጣት ማስፈጸሚያ ዘዴ ለመጠቀም በህጋቸው አጽድቀዋል። አምስት የመገናኛ ብዙሃን አባላት ግድያውን ሲፈፀም ለማየት በአትሞር ወደሚገኘው ሆልማን ማረሚያ ተቋም በቫን ተሽከርካሪ ተጓጉዘዋል።

የሞት ቅጣት የተፈፀመበት ስሚዝ ከግድያው በፊት ባስተላለፈው መልዕክት “ዛሬ ማታ በአላባማ የሰው ልጅ ወደ ኋላ አንድ እርምጃ እንዲወስድ ያደርገዋል” ሲላ ተናግሯል። አክሎም “ስለረዳችሁኝ አመሰግናለሁ፡ ሁላችሁንም እወዳችኃለሁ” ሲል ተደምጧል። ጋዙ ወዳደረገው ጭምብል መፍሰስ ከጀመረ በኋላ እስረኛው ፈገግ ብሎ ወደ ቤተሰቦቹ ሲመለከት ታይቷል።

መሞቱ ከመረጋገጡ በፊት ምስክሮቹ እንደተናገሩት ከሁለት እስከ አራት ደቂቃዎች በኃይል ሲተነፍስ እንደነበረ ለአምስት ደቂቃ ያህል ከባድ ትንፋሽን መመልከታቸውን ገልፀዋል። ኦክሲጅን ከሌለ ናይትሮጅን ብቻ መተንፈስ በሰውነት ውስጥ ያሉ ሴሎች እንዲሰባበሩ እና የሰው ልጅ ወደ ሞት እንዲያመራ በፍጥነት ሊያደርገው ይችላል።